16/10/2026
የደባርቅ ጠቅላላ ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል ያለሙ ሁለት የQuality Improvement ፕሮጀክቶችን አስተወወቀ።
(ደባርቅ 6/2/18)
በደባርቅ ጠቅላላ ሆስፒታል የኳሊቲ ዲፓርትመንት አስተባባሪነት የህክምና አገልግሎት አሰጣጥን ይበልጥ ለማቀላጠፍና ጥራቱን ለማሳደግ ያለሙ ሁለት የጥራት ማሻሻያ (Quality Improvement) ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ለውይይት ቀረቡ።
በመድረኩ ላይ የቀረቡት ፕሮጀክቶች በዋናነት በሆስፒታሉ የሜዲካል ዋርድ (የተኝቶ ህክምና) እና በእናቶች ህክምና ክፍል አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው።
በዚህም መሰረት በተኝቶ ህክምና ክፍል፡ የሜዲካል ዋርድ አስተባባሪው አቶ አራጋው ሳልዬ የተኝቶ ህክምና የሚከታተሉ ታካሚዎችን የምኝታ ቆይታ ማሳጠር የሚያስችልና አገልግሎቱን ህመምተኛ ተኮር የሚያደርግ የጥራት ማሻሻያ ፕሮጀክት አቅርበዋል።
በእናቶች ህክምና ክፍል፡ የእናቶች ህክምና አገልግሎት ኦፊሰሩ አቶ ጌታው ጤና ወላድ እናቶች እንደወለዱ ወዲያውኑ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት የሚያገኙበትን፤ በተለይም የረዥም ጊዜ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን በስፋት እንዲጠቀሙ የሚያስችል ፕሮጀክት አቅርበዋል።
የመድረኩ አስተባባሪና የኳሊቲ ዲፓርትመንት ኃላፊ አቶ ደምሴ አዳሙ በቀረቡት ፕሮጀክቶች ላይ በሰጡት አስተያየት፤ የቀረቡት የጥራት ማሻሻያ ሀሳቦች በተግባር ላይ ሲውሉ የጎላ ለውጥ የሚያመጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቶቹ በተቀመጠላቸው የድርጊት መርሃ ግብርና የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በጥብቅ እንዲፈፀሙ አሳስበዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎች ገንቢ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።
የደባርቅ ጠቅላላ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለአምላክ ተስፋ በበኩላቸው፤ የቀረቡት ፕሮጀክቶች የታካሚዎችን እንግልቶና የእናቶችን ሞት የሚቀንሱና በርካታ ክፍተቶችን የሚሞሉ ችግር ፈች ስራዎች መሆናቸውን ገልፀዋል። አክለውም ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ተተግብረው ግባቸውን እንዲመቱ ሆስፒታሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ የሚያደርግ መሆኑንና ለባለሙያዎችም አስፈላጊው ስልጠና እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።